በልዩ መልክ የተዘጋጀ የንግድ ስራ ፈጠራ ስልጠና

በልዩ መልክ የተዘጋጀው የንግድ ስራ ፈጠራ ስልጠና ዝቅተኛ የመደበኛ ትምህርት ደረጃ ያላቸውን የንግድ ስራ ፈጠራ ሰዎችን  እና/ወይም ውስን የንግድ ስራ ልምድ ያላቸው ግለሰቦች ላይ ትኩረት ያደረገ የሁለት ቀን ስልጠና ነው፡፡ ይህ የስልጠና መርሃግብር አለም ላይ ያሉ ስኬታማ የንግድ ስራ ሰዎች ያሏቸውን ግለሰባዊ ንግድ ስራ ፈጠራ ብቃቶች እና ተያያዥነት ያላቸውን ባህርያት በመጭመቅ ለተሳታፊዎች የተዘጋጀ ባህሪያዊና የአመለካከት ለውጥ የሚያመጣ መርሃግብር ነው፡፡

ይህ ስልጠና ከኢ.ቲ.ደብሊው ተወስዶ በልዩ መልክ የተዘጋጀ እንደመሆኑ በኢ.ቲ.ደብሊው ስልጠና ላይ የሚተገበሩ የማሰልጠኛ ዘዴዎች ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡ በመሆኑም  ይህ በልዩ መልክ የተዘጋጀው ስልጠና የአዋቂ ሰዎች የመማር መርሆች ላይ መሰረት ያደረገ ተሳታፊ ተኮር፣ ተግባራዊ፣ የአመለካከትና የባህሪ ለውጥ የሚያመጣ ስልጠና ነው፡፡ አብዛኛው የስልጠና አካሄድ በተለያዩ ጥናቶች፣ በትምህርታዊ ጨዋታዎች፣ በሮል ፕሌይ፣ በልምምዶችን እና በልምድ መለዋወጫ መንገዶች አማካይነት የሚሰጥ ነው፡፡ የተሳታፊዎችን የመደበኛ ትምህርት ደረጃ ያማከለ በማድረግ የስልጠናውን ዓላማ ለማሳካት ቀለል ተደርጎ የተዘጋጀ ስልጠና ነው፡፡

በስልጠናው የሚጠበቅባቸውን አስፈላጊ ሁኔታዎች በብቃት የሚያጠናቅቁ ተሳታፊዎች የተሳትፎ የምስክር ወረቀት ይሰጣቸዋል፡፡ አስፈላጊ ሁኔታዎቹ በ2ቱ የስልጠና ቀናት ሙሉ ተሳትፎ ማድረግ እና የተለያዩ የሚሰጡ ስራዎችን በብቃትና በስኬት ማጠናቀቅን ያካትታል፡፡           የአሰልጣኞች ስልጠና

ይህ የአሰልጣኞች ስልጠና አሰልጣኝ መሆን የሚያስችል አቅም ያላቸውን ዕጩ ሰልጣኞች የስልጠና አቅማቸውን ለመገንባት ታስቦ የሚሰራ አካሄድ ነው፡፡ በመሆኑም ሂደቱ ዕጩ አሰልጣኞችን መለየትና ተከታታይ የስልጠና መርሃግብሮች ውስጥ እንዲያልፉ እና ስልጠናዎችን በሙሉ ብቃት ለንግድ ስራ ፈጣሪዎች መስጠት እንዲችሉ የተግባር ማሳያ ውስጥ እንዲያልፉ ይደረጋል፡፡

ይህ የአሰልጣኞች ስልጠና የዕጩ አሰልጣኞችን ስልጠና የመስጠት ክህሎት መጨመር በሚያስችል መልኩ ልምድ ላይ መሰረት አድርጎ ይሰጣል፡፡ ንድፈ ሃሳባዊ የኣዋቂ ሰዎች የመማርያ መርሆዎችን ተግባር ተኮር ከሆነ ስልጠና የመስጠት ክህሎቶችን ከሚያጎለብት የተግባር ማሳያ መርሃግብር ጋር ተጣምሮ ይሰጣል፡፡ ስልጠናው የሚከተሉትን አካሄዶች መከተል ይኖርበታል፡-  

ሂደት 1፡ ዕጩ አሰልጣኙ/ኟ የኢ.ቲ.ደብሊው ስልጠናን መውሰድ ይኖራባቸዋል፡፡ በስልጠናው ወቅት በሚያሳየው/በምታሳየው ውጤት መሰረት ተሳታፊው/ዋ ብቁ አሰልጣኝ ለመሆን ወደሚያስችሉ ቀጣይ ስልጠናዎች የመሳተፍ ዕድሉን ማግኘት እንዲችሉ የአሰልጣኞች ቡድን ምስክርነት ያስፈልጋል፡፡ ይህን ዕድል ተጠቃሚ የሚሆኑት አሰልጣኝ ለመሆን የተቀመጠውን ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ የሚያሟሉ ተሳታፊዎች ናቸው፡፡

ሂደት 2፡ አሰልጣኝ መሆን የሚያስችል አቅም እንዳለው/እንዳላት ምስክርነት ያገኘው/ችው ዕጩ አሰልጣኝ በስልጠና ክፍል የሚደረግለትን/የሚደረግላትን የቃለ ምልልስ ክፍለ ጊዜ በብቃት ማለፍ ይኖርበታል/ይኖርባታል፡፡

ሂደት 3፡ የቃለ ምልልስ ክፍለጊዜውን ማለፍ የቻሉ ዕጩ አሰልጣኞች የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ባለው አሰልጣኝ ክትትል ስር በመሆን 2 የተግባር ልምምድ ስልጠና ክፍለ ጊዜያት ውስጥ ማለፍ ይኖርባቸዋል፡፡ በመቀጠል ዕጩ አሰልጣኙ/ኟ ልቀው መውጣት ከቻሉ የአሰልጣኞች ስልጠና ተካፋይ መሆን እንደሚችሉ ማረጋገጫ ይሰጣቸዋል፡፡

ሂደት4 ፡ ይህ ሂደት ዕጩ አሰልጣኙ/ኟ ከአዋቂ ሰዎች የመማርያ መንገድ ፍልስፍናዎች እና የማሰልጠኛ ዘዴዎች፣ የአቀራረብ ክህሎቶች፣ ከአሰልጣኝ መመሪያዎች፣ ልምምዶች እንዲሁም ከተለያዩ የማሰልጠኛ ጥናቶች ጋር ትውውቅ የሚያደርጉበት የአሰልጣኞች ስልጠና መርሃግብር ውስጥ ይወስዳቸዋል፡፡ እንዲሁም ዕጩ ሰልጣኞች የሚመለመሉበት መንገድ እና ማህደራቸው ስለሚያዝበት አሰራር እና ለስልጠናው ሂደት እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ይማራሉ፡፡

ሂደት 5፡ ይህንን መርሃግብር በውጤታማነት የሚያጠናቅቁ አሰልጣኞች በማስተር አሰልጣኞች ክትትልና እገዛ ስር በመሆን 4 የስልጠና ክፍለ ጊዜዎች ውስጥ ይመደባሉ፡፡ በመቀጠልም የናሽናል አሰልጣኝነት የምስክር ወረቀት ለማግኘት 6 የስልጠና ክፍለ ጊዜያትን በመጠነኛ ክትትል ስር በመሆን በውጤታማነት መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህም የምስክር ወረቀት ባለው/ባላት ናሽናል አሰልጣኝ፣ ማስተር አሰልጣኝ፣ ወይም ኢንተርናሽናል አሰልጣኝ አማካኝነት የሚሰጠውን የፈተና መርሃግብር በስኬት ማለፍን ይጠይቃል፡፡

የናሽናል አሰልጣኝነት የምስክር ወረቀት ካገኙ በኋላ አሰልጣኙ/ኟ የአሰልጣኞችን የምስክር ወረቀት አሰጣጥ ሂደት መመሪያዎችን በመጠበቅ የአሰልጣኝነት የስራ ህይወታቸውን ወደ ቀጣይ ደረጃ ማሳደግ ይችላሉ፡፡ ኢ.ዲ.ሲ ከአጋሮቻችን ጋር በትብብር በመስራት መርሃግብሩን በስኬት በማጠናቀቅ የስልጠና መስፈርቶቹን ላሟሉ ዕጩዎች በሁሉም የአሰልጣኞች ስልጠና ሂደቶች ውስጥ የተሳትፎ ምስክር ወረቀት ይሰጣል፡፡       


የንግድ ስራ ማጎልበት እገዛ አገልግሎት ሰጪዎች ስልጠና


ይህ ስልጠና የመነጨው የንግድ ስራ ፈጠራ ማጎልበት ጅማሮ ስኬታማነት ከስልጠና በኋላ ለንግድ ስራ ፈጠራ ሰዎች በሚሰጠው ድጋፍ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ከመገንዘብ በመነሳት ነው፡፡ የድርጅቶች የንግድ ስራ ፈጠራ አቅምና ዕድገት በልዩ ሁኔታ በተዘጋጁ ተጨማሪ የአስተዳደር ክህሎቶች ስልጠና/ማማከር አገልግሎቶች አማካኝነት በይበልጥ ይጨምራል፡፡

ይህንንም ዕውን ለማድረግ ኢ.ዲ.ሲ የኢ.ቲ.ደብሊው ስልጠናን በስኬት የተከታተሉ የንግድ ስራ ፈጠራ ሰዎች ባሉበት አካባቢ የሚገኙ የንግድ ስራ ማጎልበት አማካሪዎችን መልምሎ ያሰለጥናል፡፡ የንግድ ስራ ፈጠራ ሰዎች የስልጠናውን መርሃግብር በስኬት ካጠናቀቁ በኋላ ልምድ ባላቸው ነባር የንግድ ስራ ማጎልበት አማካሪዎች የሚሰጠውን የንግድ ስራ ማጎልበቻ ድጋፍ ሰጪዎች አቅም ማሻሻያ ስልጠና መውሰድ ይችላሉ፡፡

የስልጠናው መርሃግብር በንግድ ስራ ውስጥ እንዲሁም ለደንበኞች የማማከር አገልግሎት በመስጠት ሂደት ውስጥ ከተገኙ ትምህርቶች የተወሰዱ አሳታፊ የሆኑ የክፍል ውስጥ ክፍለ ጊዜያትን ያካተተ ለ6 ቀናት የሚቆይ የስልጠና መርሃግብር ነው፡፡ የክፍል ውስጥ ክፍለ ጊዜያቱ ሰልጣኞች በነባር የንግድ ስራ ማጎልበት አማካሪ ክትትል ስር በመሆን ደንበኞች ተመድበውላቸው አገልግሎት የሚሰጡበት ለሳምንት የሚቆይ የማማከር መርሃግብር ጋር ተጣምሮ ይሰጣል፡፡

የስልጠናው ርዕሶች ይዘት የንግድ ስራ ጤናማነት ምርመራ፣ የንግድ ስራ ዕቅድ አወጣጥና ግምገማ/ክለሳ፣ የንግድ ስራ ማማከር፣ ስራዎችን ለሌሎች በስምምነት ሰጥቶ የመስራት አማራጭ፣ የገንዘብ ነክ ጉዳዮች ትንተናና አስተዳደርን የመሳሰሉ መሰረታዊ የንግድ ስራ አስተዳደር ክህሎቶችን ያካትታል፡፡ ስልጠናው የሚከተሉትን አካሄዶች መከተል ይኖርበታል፡-

ሂደት 1፡ ዕጩ አማካሪው/ዋ የኢ.ቲ.ደብሊው ስልጠና መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡ በስልጠናው ወቅት በሚያሳየው/በምታሳየው ውጤት መሰረት ተሳታፊው/ዋ የንግድ ስራ ማጎልበት ድጋፍ አገልግሎት ሰጪ ለመሆን ወደሚያስችሉ ቀጣይ ስልጠናዎች የመሳተፍ ዕድሉን ማግኘት እንዲችሉ የአሰልጣኞች ቡድን ምስክርነት ያስፈልጋል፡፡ የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ለመሆን የተቀመጠውን ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ማሟላት ይጠይቃል፡፡      

ሂደት 2፡ የአሰልጣኞች ቡድን ምስክርነት ያገኘው/ችው ዕጩ በንግድ ስራ ማጎልበት አገልግሎት ሰጪ ክፍል የሚደረግለትን/የሚደረግላትን የቃለ ምልልስ ክፍለ ጊዜ በብቃት ማለፍ ይኖርበታል/ይኖርባታል፡፡  

 

ሂደት 3፡ የቃለ ምልልስ ክፍለ ጊዜውን ማለፍ የቻለ/የቻለች ዕጩ የንግድ ስራ ማጎልበት አገልግሎት አሰጣጥ መሰረታዊ መርሆች ላይ በሚሰጠው የ5 ቀናት የክፍል ውስጥ ስልጠና ማለፍ ይኖርባቸዋል፡፡              

ሂደት4 ፡ የክፍል ውስጥ ስልጠናውን በውጤታማነት ያጠናቀቀ/ያጠናቀቀች ዕጩ በነባር የንግድ ስራ ማጎልበት አገልግሎት ሰጪ ክትትል ስር በመሆን ወደ ዕውነታዊው/ተግባራዊው የማማከር አገልግሎት መርሃግብር ውስጥ ይሳተፋል/ትሳተፋለች፡፡   

   • +251-115-571-150
  • Cette adresse e-mail est protégée contre les robots spammeurs. Vous devez activer le JavaScript pour la visualiser.
© 2022. All Rights Reserved. EDC-Ethiopia

We use cookies to improve your experience on our website. By browsing this website, you agree to our use of cookies.